ለበልግ ምርት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ የባቢሌ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡

ለበልግ ምርት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ እንደሚገኙ የባቢሌ ወረዳ አርሶ አደሮች ገለፁ፡፡

   የበጋው ወቅት አልፎ ክረምቱ ሊተካ ጥቂት ግዜያት ይቀሩታል፤ዝናብን ጠብቆ ዘሩን የሚበትነው አብዛኛው የሀገሬ ገበሬም ለበልግ ሰብሉ የክረምቱን ዝናብ ውሃ ለመጠቀም የበጋው ወቅት ላይ መሬቱን ማለስለስ ይጀምራል፡፡

 

ከሀረሪ ብዙሀን መገናኛ ኤጀንሲ ጋር ቆይታ የነበራቸው የባቢሌ ወረዳ አርሶ አደሮችም ፤ከበልግ ምርታቸው ጠቀም ያለ ምርት ለመሰብሰብ በማለም አስቀድመው ቅድመ ዝግጅታቸውን እያጠናቀቁ እንደሆነ ነግረውናል፡፡

 

የሐገር ዋልታ የሆነው አርሶ አደር ከራሱ አልፎ ከተማውን ለመመገብ ብዙ ጥረት ቢያደርግም ማዳበሪን የመሳሰሉ ግብዓቶች ካልተሟሉ ውጤታማ የሚሆንበት እድል ይጠባል፡፡

 

ለዚህም መንግስት ምርጥ ዘርና የማዳበሪያ አቅርቦት በተመጣጣኝ ዋጋ ከማቅረብ ባሻገር የግብርና ባለሞያዎችን መድቦ ዘርፉን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡

 

ይሁን እንጂ ከዚህ ቀደም የግብዓት አቅርቦቱ አርሶ አደሩ በሚፈልገው ልክና ወቅት የማይቀርብ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ችግሮች ሲያጋጥሙ ቆይቷል፡፡

 

በዚህ አመት ግን ይህ ችግር እንዳይገጥም  የተለያዩ እንቅስቃሴዎች ሲያደርግ እያየን ነው የሚሉት አርሶ አደሮቹ የዋጋው ነገር ግን ሊታሰብበት ይገባል ይላሉ፡፡

 

በዘንድሮው የበልግ ወቅት በርካታ ሰብሎችን በክላስተር ለማምረት አቅደናል የሚሉት የወረዳው የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ፅህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ጫላ ጣሀ ከምርጥ ዘር አቅርቦት ጋር ተያይዞ ከአፍረን ቀሎ ዩኒየን ጋር በመተባበር በተሰራው ስራ እጥረት ሊያጋጥም በማይችል ልኩ ተዘጋጅተናል ብለዋል፡፡

 

ለዘንድሮው የበልግ ምርት ዘጠኝ ሺ ኩንታል ማዳበሪያ ያስፈልጋል የሚሉት አቶ ጫላ ከዚህም አብዛኛውን አስቀድመን አስገብተናል ይላሉ፡፡

 

ከማዳበሪያና ምርጥ ዘር ዋጋ ጋር ተያይዞ የተነሳው ቅሬታ ተገቢ ነው የሚሉት አቶ ጫላ በሀገር አቀፍ ደረጃ ትልቅ እጥረት ቢኖርም ከፌደራል በተቀመጠ አቅጣጫ መሰረት ሁሉም አርሶ አደር መግዛት በሚችልበት ዋጋ እንዲሸጥ ይደረጋል ብለዋል፡፡

 

ዘጋቢ ሄኖክ ዘነበ

27 7 13