በሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ እና ምክትል ርእሰ መስተዳደር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ የተመራው የክልሉ ካቢኔ አባላት የፕሮጀክቶች ግንባታ አፈጻጸም የመስክ ጉብንት ተጠናቀቀ፡፡

በሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ እና ምክትል ርእሰ መስተዳደር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ የተመራው የክልሉ ካቢኔ አባላት የፕሮጀክቶች ግንባታ አፈጻጸም የመስክ ጉብንት ተጠናቀቀ፡፡

  ባሳለፍነው ቅዳሜ የተጀመረው የሀረሪ ክልል ካቢኔ አባላት በክልሉ በገጠርና ከተማ በመካሄድ ላይ የሚገኙ  የፕሮጀክቶ ግንባታ አፈጻጸም የመስክ ጉብኝትና ግምገማ በትላንትናው  እለት ቀጥሎ የተካሄደ ሲሆን የአውበርከሌ 2ኛ ትውልድ የጤና ኬላ ግንባታ፤የአውጀይላን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ ፤የመንፈሳዊ 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ፕሮጀክት አፈፃፀም፤የሪጅናል ላብራቶሪ ፕሮጀክት ግንባታ  አፈጻጸምንና የመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት ፕሮጀክት አፈጻጸምን ነው የካቢኔ አባላቱ ተዘዋውረው የጎበኙት፡

   በዚህም በ11 ሚሊዮን ብር በሶፊ ወረዳ አውበርከሌ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ተገንብቶ በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የአውበርከሌ 2ኛ ትውልድ ጤና ኬላን ቀሪ ስራዎችን በፍጥነት በማጠናቀቅ እና ግብዓቶችን በማሟላት አገልግሎት ማስጀመር ያስፈልጋል ያሉት የሐረሪ ክልል ርእሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪ ጤና ኬላውን ገንብቶ እውን ከማድረግ ጎን ለጎን የውሃ፤የመብራት፤የመንገድና የትምህርት ቤቶች መሠረተ ልማቶችንም ማከናወን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

   የአውበርከሌ ጤና ኬላ የክልሉ መንግስት የገጠር ነዋሪዎች ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን ለማስፋት ለሰጠው ትኩረት ማሳያ ይሆናል ያሉት ርእሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት ለጤና ኬላው አገልግሎት አሰጣጥ የሚሆን  የተማረ የሰው ሀይል ለማሟላት ዝግጁ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

  በቀበሌው ነዋሪዎች ተሳትፎ የተሰራው 15ኪ.ሜ የሚሸፍነው የጥርጊያ መንገድ ስራም የጉብኝቱ አንድ አካል የነበረ ሲሆን የመንገዱን ደረጃ ለማሳደግ የክልሉ መንግስት በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራ ተገልጻል፡፡

   ሌላው የክልሉ ካቢኔ አባላት የጉብኝት አካል የሆነው በ9 ሚሊዮን ብር በጀት  ግንባታው ባሳለፍነው አመት ግንቦት ወር ላይ ተጀምሮ አሁን ላይ ግንባታው 40 በመቶ የተጠናቀቀው  የአውጀይላን 1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አንዱ ሲሆን አጥር እና የመፀዳጃ ቤትን ጨምሮ 12 የሚሆኑ የመማሪያ ክፍሎችን አጠቃሎ የያዘ እና ግንባታው ሰኔ 2013 ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተገልጻል፡፡

   በ15 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ወጪ ባሳለፍነው አመት የተጀመረው የመንፈሳዊ ባለ አራት ፎቅ  1ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ግንባታ በአሁኑ ግዜ 40 በመቶ እንደተጠናቀቀም በጉብኝቱ ወቅት ከተደረገው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል፡፡

   ሌላው የክልሉ ካቢኔ አባላት የአፈፃፀም ጉብኝት አካል የነበረው እና በኢ.ፌ.ድ.ሪ ጤና ሚኒስቴርና በክልሉ ጤና ቢሮ ባለቤትነት ከ2010 ጀምሮ በመገንባት ላይ የሚገኘው የሪጅናል ላብራቶሪ ባለ ሁለት ፎቅ ህንጻ ግንባታ ይጠናቀቃል ተብሎ ከተያዘለት ግዜ እጅግ የዘገየ መሆኑና በአጭር ግዜ ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችሉ ስልቶች ተቀይሰው ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡

  በ20 ሚሊዮን ብር በጀት በመገንባት ላይ የሚገኘው 40 ቤቶችን የያዘው የመምህራን የጋራ መኖሪያ ቤት  ባለ አራት ፎቅ  ህንጻ ግንባታ ፕሮጀክት በክልሉ የሚገኙ መምህራን የብዙ ግዜ ጥያቄ የነበረውን የቤት ችግር ለማጠቃለል የተጀመረ መሆኑ በጉብኝቱ ወቅት ተገልፃል፡፡

   ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የክልሉ ካቢኔ አባላት በገጠርና በከተማ የሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች አፈፃፀም የመስክ ጉብኝት በትላንትናው እለት የተጠናቀ ሲሆን የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እና ምክትል ርእሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሚስራ አብደላ እንዳሉትም የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች ግብዓቶች ተሟተውላቸው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙት ፕሮጀክቶች ቀሪ ስራዎችን በአጭር ግዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ቅንጅታዊ ጥረት ማድረግ እንደሚስልግና በተለያየ ምክንያቶች የዘገዩት ፕሮጀክቶች ላይ ደግሞ የማስተካከያ እርምጃዎችን በመውሰድ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ እንደሚስልግም አቅጣጫ አስቀምጠዋል፡፡

ዘጋቢ ሄኖክ ግርማ 
26 5 13