በበልግ ምርት 21 ሺ 210 ሄክታር መሬትን ለመሸፈን እየሰራ እንደሚገኝ የባቢሌ ወረዳ የግብርና እና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በበልግ ምርት 21 ሺ 210 ሄክታር መሬትን ለመሸፈን እየሰራ እንደሚገኝ የባቢሌ ወረዳ የግብርና እና  የተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

 በዘንድሮ የበልግ ምርት 21 ሺ 210 ሄክታር መሬት በሰብል ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን ከዚህ ውስጥም የአርሶ አደሩን ምርታማነትና ተጠቃሚነት ለማሳደግ በሰብል ለመሸፈን ከታቀደው የእርሻ መሬት ውስጥ ከ60 በመቶ በላይ  የሚሆነውን በክላስተር ለማልማት መታቀዱ ነው የተገለፀው ፡፡

 

 ለዚህም  ያመች ዘንድ በአራት ክላስተር ተከፋፍለው ለማልማት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ ነው የወረዳው ግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ልማት ፅህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ አቶ ጫላ ጠሃ ለሀረሪ ብዙሀን መገናኛ ኤጀንሲ የተናገሩት ፡፡

 

በክላስተር ለማልማት ከታቀደው 12 ሺ ሄክታር መሬት ውስጥም ስድስት ሺ ሄክታር መሬት በማሽላ፤ሶስት ሺ አርባ ሄክታር መሬት በበቆሎና አንድ መቶ ሀምሳ ሄክታር መሬት በቆሎ ፤ስንዴ የሚሸፈን ሲሆን ቀሪው መሬት ደግሞ በወረዳው በስፋት በሚመረተው በለውዝ ምርት ይሸፈናል ብለዋል፡፡

 

ከዚህ ቀደም በወረዳው የስንዴ ምርት አልነበረም የሚሉት ምክትል ሀላፊው አሁን ግን እደሀገር ከውጪ የሚመጣውን ስንዴ ለማስቀረት በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ወረዳው  በዘንድሮው የበልግ ምርት ስንዴን በክላስተር ለማልማት ማቀዱንና ከታቀደው 150 ሄክታር መሬት ውስጥ አምሳ ሄክታር ያህል ተዘጋጅቷል ብለዋል፡፡

 

በክላስተር ለማልማት የታቀደው እቅድ ግቡን እንዲመታ ከግብርና ኤክስቴንሽን ባላሞያዎች እስከታች አርሶ አደሩ ድረስ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል ተብሏል፡፡

 

የምርጥ ዘርና የማዳበሪ አቅርቦትንም በተሻለ ሁኔታ በሚፈለገው እና ወቅት ልክ ለማድረስም መጠነ ሰፊ ስራዎችን ተሰርተዋል  ብለዋል፡፡

 

ከዚህ ባሻገርም በባለፈው አመት ለወረዳው ተሰጥተው አሁን ላይ ወደተለያዩ ወረዳዎች በውሰት የሄዱ አስራ ሶስት ትራክተሮችንም ወደ ወረዳው እንዲመለሱና ዝግጁ እንዲሆኑ መደረጉን አቶ ጫላ ጠሃ ተናግረዋል፡፡

 

ከትራክተር  ታሪፍ ጋር ተያይዞ የተለያዩ ቅሬታዎችን ይነሱ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ጫላ ይህንንም ችግር ከወረዳው ንግድ ልማት ፅህፈት ቤት ጋር በመተባበር ፈተናል ብለዋል፡፡

 

አርሶ አደሩ የራሱን የምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ አልፎ ለሀገር እንዲተርፍ  ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካል ከጎኑ እንዲቆም አቶ ጫላ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

 

ዘጋቢ ሄኖክ ዘነበ

22 7 13