በአለም ባንክ ድጋፍ የእንጨት ፓሎችን ወደ ኮንክሪት ፓሎች የመቀየር ሥራ በይፋ መጀመሩን የሀረሪ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

በአለም ባንክ ድጋፍ የእንጨት ፓሎችን ወደ ኮንክሪት ፓሎች የመቀየር ሥራ በይፋ መጀመሩን የሀረሪ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽ/ቤት አስታወቀ፡፡

የሀረሪ ክልል የመብራት ሀይል አገልግሎት የኮሚኒኬሽን ስራ አስኪያጅ አቶ ሰንታየሁ መላኩ ለሀረር ኤፍ ኤም 101.4 እንደገለፁት በመጀመሪያው ዙር የሀገሪቱን ስድስት ከተሞችን ተጠቃሚ የሚያደርገውና ለረጅም አመታት አግልግሎት ሲሰጡ የነበሩትን የእንጨት የኤሌክትሪክ ፖሎችን ወደ ኮንክሪት ፖሎች የሚቀይረው ፕሮጀክት በሀረሪ ክልል ባሳለፍነው መጋቢት ወር በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል፡፡

 

በዚሁም ወደ 87 ኪ.ሜትር ከፍተኛ መስመሮችና ወደ 73 ኪ.ሜ ዝቅተኛ መስመሮች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የእንጨት ፖሎች ወደ ኮንክሪት ፖሎች እንደሚቀይሩም ነው አቶ ስንታየሁ የገለፁት፡፡

 

በሌላ በኩል በከተማው የሚገኙ 14 የሚሆኑ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ትራንስፎመሮችን የማሻሻል ስራም የዚህ ፕሮጀክት አካል መሆኑን የጠቆሙት አቶ ስናንታየሁ 20 የሚሆኑ አዲስ የአሌክትሪክ ማስተላለፊያ  ትራንስፎርመሮች እንደሚተከሉ ገልጸው ይህም ደግሞ በተደጋጋሚ ጊዜ የሚስተዋለውን የአሌክትሪክ መስመር መቆራረጥና በሰዎች ላይ የሚደርሰውን የአካል ጉዳት እና ሞት ለመቅረፍ የሚኖረው አበርክቶ የጎላ ነው ይላሉ፡፡

 

ፕሮጀክቱ ለ200 ስራ አጥ ዜጎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ነው የተገለፀው

 

በአለም ባንክ ድጋፍ በ200 ሚሊየን ብር የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት የክልሉን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ከፍ እንደሚያደርገውም ነው አቶ ስንታየሁ ያስተዋወቁት፡፡

 

ይህ የእንጨት ፖሎችን ወደ ኮንክሪት ፖሎች የሚቀይረው ፕሮጀክት በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ሕብረተሰቡ በቀናነትና በእኔነት ስሜት አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል፡፡

 

ባሳለፍነው መጋቢት ወር የተጀመረው ይህ ፕሮጀክት በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ከክልሉ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ሄኖክ ግርማ

4 8 13