በ6ተኛው ሐገራዊ ምርጫ በሁለንተናዊ መልኩ ለመሳተፍ ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ አለ የሐረሪ ክልል አካል ጉዳተኞች ጥምረት ማህበር ፡፡

በ6ተኛው ሐገራዊ ምርጫ በሁለንተናዊ መልኩ ለመሳተፍ ዝግጅቴን አጠናቅቄያለሁ አለ የሐረሪ ክልል አካል ጉዳተኞች ጥምረት ማህበር ፡፡

የሐረሪ ክልል አካል ጉዳተኞች ጥምረት ማህበር በይፋ ከተመሠረተ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን የአካል ጉዳተኞችን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ የተለያየ ስራዎችን ሲሰራ ነበር የሚሉት የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ሚካኤል ዩሐንስ በተለይ ማህበራዊ መናጋት ያስከተለው የኮሮና  ቫይረስ በአካል ጉዳተኛው ላይ የከፋ ተፅኖ ማድረሱን ጠቁመው ይህን ለመቅረፍ ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ድጋፍ እስከመስጠት መድረሱን ያስታውሳሉ፡፡

 

በግንቦት ወር ላይ የሚካሄደው 6ተኛው ሀገራዊ ምርጫ ላይ ተሳታፊ ከመሆን አንፃር የአካል ጉዳተኞች ሚና ምን መሆን አለበት በሚለው ዙርያ ከሀረሪ ብዙሀን መገናኛ ኤጀንሲ ጋር ቆይታ ያደረጉት ፕሬዝዳንቱ አባላቱ ሁለንተናዊ ዝግጅት ማድረጋቸውን ጠቁመዋል፡፡

 

አካል ጉዳተኝነት ማለት አለመቻል አለመሆኑን የገለፁት አቶ ሚካኤል የመምረጥም ሆነ የመመረጥ መብታቸውን ማስጠበቅ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡

 

ምርጫ ቦርድም በተለይ መስማት የተሳናቸውንና አይነስውራንን ማእከል ያደረገ ስራ ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

 

ምርጫ እና መሠል ሁነቶች ጎላ ብለው በሚታዩበት ወቅት ብቻ ነው ፖለቲካ ፖርቲዎችን ጨምሮ ሌሎችም ስለ አካል ጉዳተኞች ትዝ የሚላቸው የሚል ሁሌም ከአካል ጉዳተኞች የሚነሳ ቅሬታ ነው፡፡

 

 ምንም እንኳ በያዙት ፖሊሲዎቻቸው እነርሱን ማእከል ያደረገ ስራ ለመስራት እቅድ ይዘናል ቢሉም ከምርጫው ሁነት በኋላ ግን የሚያስታውሳቸው እንደሌለም ብዙ ግዜ ሲያነሱ  ይደመጣሉ፡፡

 

 ከዚህ አንፃር ማህበራችሁን ያነጋገረ ፖርቲ ይኖር ይሆን ስንል ላነሳው ጥያቄ ፕሬዘዳንቱ በምላሻቸው እኛ እየጠበቅናቸው ቢሆንም ፓርቲው ባሉ ሰዎች በግለሰብ ደረጃ ካላ ከግለሰቡ ድጋፍ ውጭ እንደፓርቲ እስካሁን ያነጋገረን የለም ሲሉ መልሠዋል፡፡

 

በምርጫው ሂደት ያላቸውን ተሳትፎ ይበልጥ ለማጎልበት ከኢትዮጵያ የአካል ጉዳተኞች ፌደሬሽን በቀረበ ጥያቄ የተለያዩ አባላትን ለስልጠና መላኩን ያመላከተው የሐረሪ ክልል አካል ጉዳተኞች ጥምረት ማህበር በሁለንተናዊ መልኩ በምርጫው ከመሳተፍ ባለፈ የአካል ጉዳተኛውን ጥቅም ለማስጠበቅ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡

ዘጋቢ ወንድሙ  አዱኛ

23 7 13