የሐረሪ ክልል ግብርና ልማት ቢሮ ከአዳፕቴሽን ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ 2 ትራክተሮችን ለተደራጁ 2 አርሶ አደር ማህበራት ሰጠ፡፡

የሐረሪ ክልል ግብርና ልማት ቢሮ ከአዳፕቴሽን ፈንድ በተገኘ የገንዘብ ድጋፍ 2 ትራክተሮችን  ለተደራጁ 2 አርሶ አደር ማህበራት ሰጠ፡፡

  በ1.5 ሚሊየን ብር የታገዘው ሁለት የማረሻ ትራክተሮች  በሲ አር ጂ ፕሮጀክት በአዳፕቴሽን ፈንድ የገንዘብ ድጋፍ የተገኘ ሲሆን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር እና የግብርና ልማት ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ለሁለት  ማህበራት ተወካዮች አስረክበዋል፡፡

 

ማህበራቱ በሶፊ ወረዳ ከሶፊ እና ቡርቃ  ቀበሌ የተደራጁ ሲሆን እያንዳንዱ ማህበር 30 አባላትን የያዙ ናቸው ፡፡

 

 ፈንዱ ተዘዋዋሪ የብድር ፈንድ በመሆኑ አርሶ አደሮቹ በዚህ ትራክተር አርሰው ጉልበታቸው እና ግዜያቸውን  ቆጥበው ከዚህ ቀደም ከሚያመርቱት የተሻለ ምርትን በማግኘት ለሌሎች መሰል አርሶ አደሮች ትራክተሮች መግዛት እንዲያስችል በተሰጣቸው የግዜ ገደብ ብሩን ለመመለስ ሊሰሩ እንደሚገባ የሀረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር እና የግብርና ልማት ቢሮ ሀላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ገልፀዋል፡፡

 

 ወይዘሮ ሚስራ አክለውም ይህን መሰል አርሶ አደሩን የመደገፍ ስራዎች የበለጠ ለልማት የሚያነሳሳ መሆኑን ጠቅሰው አረንጓዴ አሻራ ልማትን ለማረጋገጥም ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለውም ጠቁመዋል፡፡

 

  በብደር መልክ የሚሰጡ ድጋፎች የመመለስ ባህሉ ደካማ መሆኑን የጠቆሙት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሯ በመሆኑም በዛሬ እለትም አርሶ አደሩ የተበደሩትን በመውሰድ ለሌሎች አርሶ አደሮች ተጠቃሚነት የበኩላቸውን እንዲወጡ ማስገንዘባቸውን ተናግረዋል፡፡

 

  ይህን የተገዛላቸውን ትራክተር ማግኘት የቻሉት በማህበር ተደራጅተው የሚጠበቅባቸውን ቅድመ ቁጠባን በመፈፀማቸው በመሆኑ ሌሎች አርሶ አደሮችም መንግስት ባመቻቸላቸው እድል በመጠቆም በማህበር በመደራጀት ቁጠባ ፈፅመው የእድሉ ተጠቃሚ እንደሆኑ ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ገልጸዋል፡፡

 

  የመጀመሪያ ዙር እድል ተጠቃሚ በመሆናቸው የተሰማቸውን ደስታ የገለፁት አርሶ አደሮች በተሰጣቸው የ5 ዓመት የግዜ ገደብ ውስጥ በአግባቡ ከፍለው በማጠናቀቅ ሌሎች አርሶ አደሮች በቀጣይ ለሚደረጉ ድጋፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንዲያስችል የሚጠበቅባቸው እንደሚወጡ  ተናግረዋል፡፡

 

  በአሁኑ ወቅት መንግስት ለአርሶ አደሩ ለሚያደርገው ሁለንተናዊ ድጋፍም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

 

ዘጋቢ ቤተልሄም ደሴ

23 7 13