የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን 20ኛ አመት ምስረታ በማስመልከት በ9ኛ እና 11ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በፌደራል ደረጃ ግንቦት 16 ፈተና እንደሚካሄድ ተገለፁ፡፡

የስነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን 20ኛ አመት ምስረታ በማስመልከት በ9ኛ እና 11ኛ ክፍል ተማሪዎች መካከል በፌደራል ደረጃ ግንቦት 16 ፈተና እንደሚካሄድ ተገለፁ፡፡

ፈተናው ዛሬ ሚያዝያ 1 በትምህርት ቤቶች ደረጃ ተጀምሯል፡፡

 

የኮሚሽኑን 20ኛ አመት የምስረታ በዓል በማስመልከት የስነ ምግባር ፈተና በ9ኛ እና 11ኛ ክፍል እንዲሁም ከመንግስት ኮሌጆችና ከግል ኮሌጆች እንዲሁም ከዩኒቨርሲቲዎች በተውጣጡ ተማሪዎች መካከል ውድድር እንደሚካሄድ የሐረሪ ክልል የስነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር ኻሊድ ኑሬ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ በሚገኙ ከ50 በላይ የሚሆኑ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የስነ ምግባር ክበብ ማቋቋም እንደተቻለም ኮሚሽነር ኻሊድ ተናግረዋል፡፡

 

እነዚህንና ሌሎች መሰል እንቅስቃሴዎችን በመከወን እና ውጤታማ ስራን በመስራት የክልሉ ስነ ምግባር ጸረ ሙስና ኮሚሽን  እንደሀገር በ4ተኛ ደረጃ ላይ ይገኛልም ብለዋል፡፡

 

ፈተናው በተቀናጀ መልኩ እንዲሰጥ የሀረሪ ክልል ትምህርት ቢሮ እና የክልሉ ስነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን በጥምረት እየሰሩ እንደሚገኙ የተናገሩት ደግሞ በክልሉ ትምህርት ቢሮ የስነ ምግባር መኮንን የሆኑት አቶ ሞገስ ማሞ ናቸው፡፡

 

ፈተናው በትምህርት ቤቶች ደረጃ እንደ ሀገር በዛሬው እለት በተመሳሳይ ሰዓትና ቀን የተሰጠ መሆኑን የገለፁት አቶ ሞገስ ውድድሩ ሴት ተማሪዎች ከሴት ተማሪዎች ጋር በተመሳሳይ ወንድ ተማሪዎችም ከወንድ  ተማሪዎች ጋር እንደሚደረግ ነው የተናገሩት፡፡

 

በዛሬው ዕለት በት/ቤቶች ደረጃ ፈተናውን መስጠት የተጀመረ ሲሆን በወረዳዎች ደረጃ ሚያዝያ 7 በክልል ደረጃ ሚያዝያ 19 በፌደራል ደረጃ ደግሞ ግንቦት 16 እንደሚካሄድ ተነግሯል፡፡

 

በዚህ መሠረትም በትምህርት ቤቶች ደረጃ የተሰጠው ፈተና በሀረሪ ክልልም በሁሉም 2ተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተሰጥቷል፡፡

 

ለፈተናው የቀረቡ ተማሪዎች በየትምህርት ቤታቸው ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡና በስነ ምግባራቸው ምስጉን የሆኑ መሆናቸውን የገለፁት አቶ ሞገስ፣ የፈተናው አላማ ሙስናን የሚጸፍና በመልካም ስነ ምግባር የታነፁ ትውልድን ለማፍራት እንደሆነ ነው የገለፁት፡፡

 

ባስተላለፉት መልዕክትም በስነ ምግባር የታነጹ እና የሀገር ተረካቢ ትውልድን ለማፍራት ሁሉም የበኩሉን መወጣት እንዳለበትም ነው የገለፁት፡፡

 

ዘጋቢ አለም ገመቹ

1 8 13