የኑሮ ውድነቱ ከፍተኛ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን የባቢሌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የኑሮ ውድነቱ  ከፍተኛ ችግር እየፈጠረባቸው መሆኑን  የባቢሌ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

በሀገር ደረጃ የተከሰተው የኑሮ ውድነት በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች  ላይ ያሳደረው ጫና ከፍተኛ መሆኑን የዘርፉ ባለሞያዎች ይገልፃሉ፡፡

 

በተመሳሳይ በተለያዩ የምግብና ሌሎች እቃዎች ላይ የተስተዋለው የዋጋ ጭማሪ ኑሮን ከባድ እንዳደረገባቸው አስተያየታቸውን ለሀረሪ ብዙሀን መገናኛ ኤጀንሲ የሰጡ የባቢሌ ወረዳ ነዋሪዎች ገልፀዋል፡፡

 

በተለይ አንዳንድ ስግብግብ ነጋዴዎች የኑሮ ውድነቱን የሚያባብስ የዋጋ ጭማሪ እና እቃ የመደበቅ ተግባር እያካሄዱ ነው ያሉት ነዋሪዎቹ ይህን በመገንዘብ መንግስት ተገቢውን ዋጋ የማረጋጋትን ገበያን የመቆጣጠር ስራ በማካሄድ እና አስፈላጊውን እርምጃ በመውሰድ የበኩሉን ድርሻ ሊወጣ ይገባል ብለዋል፡፡

 

ጉዳዩን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው  የባቢሌ ወረዳ የንግድ ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አህመድ መሀመድ አሁን እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት መንስኤ ሰው ሰራሽ ነው ይላሉ፡፡

 

ለአብነትም  በሸቀጦች ላይ በየቀኑ የሚደረገው ጭማሪ ያለ መሆኑን በተለያዩ መንገድ  ማረጋገጣቸውንና በአሁኑ ሰዓት ገበያ የሚያረጋጋ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቶ ቁጥጥር እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

 

አክለውም የገበያ ማረጋጋት ኮሚቴው ከሰባት ሴክተር የተደራጀ መሆኑንና ይህም  የፀጥታ ሴክተርን ያሳተፈ መሆኑን የተናገሩት አቶ አህመድ በምግብ ሸቀጦች ላይ የታየው የዋጋ ንረት አሁን በግንባታ እቃዎች ላይም  ከአቅም በላይ ጭማሪው ማሳየቱን ነው የገለፁት፡፡

 

ይህንን ለማረጋጋት አንድ ነጋዴ የሚሸጥበት ዋጋ ቋሚ ማድረግ እንዳለበት ለዚህም የሚረዳ  ዘመቻ እየተካሄደ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

 

ዋጋ ንረቱ የአቅርቦት ችግር ሳይሆን ነጋዴዎች የራሳቸውን ጥቅም ለማስቀደም ያደረጉት በመሆኑ በቅርብ ግዜ  በሰፊው ለማረጋጋት እየተሰራ እንዳለ  አቶ አህመድ ተናግረዋል፡፡

 

ዘጋቢ ምስክር አለማየሁ

21 7 13