የኮቪድ 19 ክትባት የወሰዱ ሰዎች ያስከትላል ተብሎ የተሰጋው የደም መርጋት አለማጋጠሙን የሐረሪ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ገለፀ፡፡

የኮቪድ 19  ክትባት የወሰዱ  ሰዎች ያስከትላል ተብሎ የተሰጋው  የደም መርጋት አለማጋጠሙን የሐረሪ ክልል ጤና ጥበቃ ቢሮ ገለፀ፡፡

ያደጉት ሀገራት ለ3ኛው ዙር የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እጅጉን ክንዱ ያበረታባቸው ቢሆንም  እንደ ኢትዮጵያ  ሌሎች ታዳጊ ሀገራት ገና በሁለተኛው ዙር እያስከተለ ያለው ተፅዕኖ እጅግ አይሏል፡፡

 

በዚህም ሀገራት የተለያዩ ማዕቀቦችንና መቆጣጠር የሚያስችሉ ደንብና መመሪያዎችን በማውጣት ላይ ይገኛሉ፡፡

 

በሀገራችን ኢትዮጵያም የቫይረሱ ስርጭት ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ እንደመጣ በየዕለቱ በበሽታው የሚሞቱና የሚያዙ ሰዎች ቁር እጅግ እየጨመረ መምጣቱ  አመላካች ነው ፡፡

 

ለዚህ ቁጥር መጨመር ዋነኛ ምክንያት  በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው መዘናጋት እና ግድ የለሽነት ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡

 

እንደ ክልል እስከ ትላንትናው እለት ድረስ ባጠቃላይ የ89 ሰዎች ህይወት ያለፈና በተለያዩ የጤና ተቋማት በርካታ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መኖራቸው እንዲሁም ከ100 በላይ ሰዎች ራሳቸውን አግልለው በቤታቸው እየቆዩ እንደሚገኙ ከክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

 

የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት አሁን ላይ ዋነኛ መፍትሄ ተብሎ የተቀመጠው ክትባት ሲሆን ኮቬቫስ በተሰኘው ጥምረት አማካኝነት  ሀገራችን ኢትዮጵያ 2.2 ሚሊየን ዶዝ አስትራ ዜኒካ ክትባቶች ማግኘቷ የሚታወስ ነው ከዚህ በተጨማሪም ከቻይና መንግስት 300 ሺ ሲኖፋም ዶዝ የኮቪድ  ክትባት አግኝታለች ፡፡

 

እንደ ክልል በሀገር አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት በቅድሚያ መከተብ ላለባቸው 3 በመቶ ለሚሆነው የህብረተሰብ ክፍል እየተሰጠ የሚገኝ ሲሆን በቅድሚያ ከቫይሩ ጋር ቀጥታ ግንንነት ላላቸው የጤና ባለሞያዎቸ እየተሰጠ እንደሚገኝ በክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ የህክምና አገልግሎት  አሰጣጥ  ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኢሊያስ ዩኒስ ተናግረዋል፡፡

 

በተለያዩ አለም ሀገራት ክትባቱ ጋር ተያይዞ የደም መርጋት ያመጣል ተብለው የሚነሱ ጉዳዮች መኖራቸውን ተናግረው እንደ ክልል እስካሁን ምንም አይነት መሰል  ጉዳዮች አለመከሰቱን    የሚናገሩት አቶ ኢሊያስ ክትባቱ መውሰድ ከሚኖረው ጉዳት ጥቅሙ የላቀ ነው እና  አስላጊ ነው ይላሉ፡፡

 

ቢቻል ሁሉንም  የህብረተሰብ ክፍላችን ተደራሽ ብናደርግ ደስታችን ነው   የሚሉት እሳቸው የክትባቱ ውድነትና በተለይ በእርዳታ መልኩ ውስን መጠን ብቻ  ከመገኘቱ ጋር ተያይዞ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ የጤና ባለሞያዎችን ቅድሚያ በመስጠት በቀጣይ ደግሞ  በየደረጃው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች እንደሚሰጥም ይናገራሉ፡፡

 

ክትባቱ የደም መርጋት ያመጣል ብለው የቆሙ ሀገራት ጭምር ከበሽታው መስፋፋትና ጉዳት አንፃር ክትባቱ ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ድጋሚ ክትባቱን መስጠት መጀመራቸውን  የጠቀሱት አቶ ኢሊያስ ዩኒስ ህብረተሰቡ በሚነዙ አሉባልታዎች እና ውዥንብሮች ባለመገዛት ክትባቱን መውሰድ  ይኖርባቸዋል ብለዋል፡፡

 

 

ዘጋቢ እዩኤል ፀጋዬ

22 7 13