የድሬ ጠያራ ሱቁል ቀበሌ ገንዳ ኢመሬ አርሶአደሮች በጉድጓድ ውሃ ተጠቅመው ለማምረት በኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት ምክንያት መቸገራቸውን ገለፁ፡፡

የድሬ ጠያራ ሱቁል ቀበሌ ገንዳ ኢመሬ አርሶአደሮች በጉድጓድ ውሃ ተጠቅመው ለማምረት በኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት ምክንያት መቸገራቸውን ገለፁ፡፡

የሐረሪ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራ መሆኑን ኣስታውቋል፡፡

 ወይዘሮ ሳፊያ ሙመድ በድሬ ጠያራ ወረዳ የተለያየ የአትክልትና ፍራፍሬ በማምረት ላይ የተሰማሩ ሲሆን እንደ ቃሪያ ፤ጥቅል ጎመን ቲማቲም ፤ካሮት ፤ሽንኩርት ፤ድንች  ባህሮ የመሳሰሉት እያመረቱ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ማዳበሪ እየተጠቀሙ እንደሚገኙ የሚናገሩት ወይዘሮ ሳሚያ ባጋጠማቸው የኤሌክትሪክ ሀይል እጥረት  ምክንያት ውሃ ከጉድጓድ ማውጣት ባለመቻሉ የተከልናቸው እፅዋቶች በመድረቅ ላይ ናቸው ብለዋል፡፡

 

ከግብርና ልማት የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት እንዳገኑ የገለፁት ወይዘሮዋ የአካባቢው አርሶ አደሮች አትክልትና ፍራፍሬ ቢያመርቱ ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ነው የገለፁት ፡፡

 

በጉልበት ሙያ ወይዘሮ ሳፊያ ሙመድን ሲረዱ ያገኛኘናቸው ሰዎች እንዳሉት  አሁን ይህንን ስራ በመስራታቸው መነሳሳት እንደፈጠረባቸው እና ከዚህ በፊት ሲሰሩ  ከነበረው ልማዳዊ አሰራር ተላቀው ልዩነት ለማምጣት መነሳታቸውን ተናግረዋል፡፡

 

የመብራት እጥረት ባያጋጥማቸው ኖሮ ያለውን ውሃ ተጠቅመው ተጨማሪ በርካታ ምርትና መሬት ማልማት እንደሚችሉ ተናግረው ያለው ጀኔሬተር በመቃጠሉ በአንድ ነጥብ አምስት ሄክታር መሬት ላይ ያለው ምርትን ጨምሮ  በወቅታዊ የዋጋ ተመን የከፈሉበት ጉልበት ያለ ጥቅም መቅረቱን ይናገራሉ፡፡

 

ጉዳዩን አስመልክቶ ያነጋገርናቸው የድሬ ጠያራ ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ረመዳን ኢድሪስ እንዳሉትም በበጋ መስኖ ለማልማት ከታቀደው 400 ሄክታር መሬት ውስጥ 420 ሄክታር ምርት ማምረት መቻሉን እና እንደ ስኳር ድንች ጎመን ቲማቲም በብዛት መከፋፈሉን ጠቅሰው  የአምና ክረምት ዝናብ መጠን ጥሩ በመሆኑም የከርሰ ምድር ውሃ በመልካም ሁኔታ ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

 

አቶ ረመዳን አክለው እንዳሉት በአንዳንድ ቀቤሌዎች መብራት ባለመግባቱና የኑሮ ሁኔታው የሚቀልበት መንገድ ከመብራት ጋር  የተቆራኘ በመሆኑ የመብራት አለመኖር በምርት እድገት ላይ ጫና እያደረሰ ይገኛል ብለዋል፡፡

 

በቀጣይ ውሃ መሳቢ ሞተር ሲመጣ በጥሩ ስራ ላይ ላሉ አርሶ አደሮች በድጋፍ መልክ በመስጠት አርሶ አደሮቹን እንደሚያግዙ ተናግረዋል፡፡

 

 

 

 

የድሬ ጠያራ ወረዳ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ፅህፈት ቤት ሀላፊ እና በወረዳው የመብራት አቅርቦት አስተባባሪ አቶ ቲፊቅ አሚን በወረዳው  ለመንገድና መብራት አቅርቦት መስፋፋት የተለያዩ ስራዎች ሲካሄድ ቆይቷል ብለዋል፡፡

 

በአካባቢው ያለውን የመብራት እጥረት ለመቅረፍ በወረዳው ከነበረው ሁለት የመብራት መስመር በተጨማሪ አንድ መስመር እንዲጨመር የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ህብረተሰቡ በሚችለው አቅሙ ከጎናችን ከሆነ በቅርቡ ችግሩ ይፈታል ብለዋል፡፡

 

የድሬ ጠያራ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታጅር ሸሜል ኡስማን በገንደ ኢመሬ የጉድጓድ ውሃን በመጠቀም ምርት እየተመረተ እንዳለ ገልፀው እስከ 30ሜትር ድረስ በመቆፈር አርሶ አደሮች ውሃ ለማውጣት እየሰሩ ያሉት ተግባር የሚያኮራ ነው ብለዋል፡፡

 

በገንደ ኢመሬ ያለው የመብራት ሀይል አቅርቦት እጥረት ከጉድጓድ ውሃ አውጥተው የሚያለሙ አርሶ አደሮች ላይ ችግር እያስከተለ መሆኑንምገልፀዋል፡፡

 

 በአካባቢው የትራንስፎርመር አቅም በመጨመር የመብራት ሀይል ችግር እንፈታለን ያሉት የወረዳው ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ታጅር ሻሚል አርሶ አደሮች ከምንግዜውም በበለጠ መንፈስ በርትተው በማምረት ለሀገራችን እድገት የበኩላቸውን  መወጣት አለባቸው ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

 

ዘጋቢ ቱራ አያና

11 8 13